ላለፉት ሁለት ቀናት ከሁሉም የኮሪደር ልማት አስተባባሪዎች ጋር በመሆን በ2ኛ ምዕራፍ በከተማችን እየለሙ የሚገኙ ስምንት ኮሪደሮችን የስራ አፈጻጸም ተዘዋውረን ገምግመናል።
የ2ኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ 135 ኪ.ሜ ርዝማኔ ያለው የመንገድ ግንባታ፣ 42 ኪ.ሜ የሚረዝም የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራ፣ 431 ሄክታር የሚሸፍን የአረንጏዴ ልማት ስራ፣ በከተማችን ያለውን የትራንስፖርት ስርዓት ለማዘመን ከምንሰራው ስራ በተጨማሪ 23,320 በላይ መኪኖችን የማስቆም አቅም ያለው የፓርኪንግና ተርሚናሎች ግንባታ፣ 112 የህዝብ የመጸዳጃ ቦታዎች ግንባታ፣ 2669 ህንጻዎች እድሳት፣ የህጻናት መጫወቻ ሜዳዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የህዝብ መዝናኛ ፕላዛዎች፣ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶችን ያካተተ ሲሆን ከ 62 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ የከተማችን ነዋሪዎች ደግሞ የስራ እድልን የፈጠረ ሰፊ ስራ ነው::
ከተማውን በመበከል የህዝቡን ጤና በመጉዳት ከፍተኛ አሉታዊ ጉዳት ሲያደርሱ የነበሩትን ህግ እና ስርዓት አዉጥተን የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓት በከፍተኛ ደረጃ እየተገበርን ነዉ። የወንዞችን ብክለት በመከላከል በኩል ጽዱ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ለመፍጠር የብክለት መከላከል ህግ ህብረተሰባችን መቀበሉን እና የየተገበረዉ መሆኑን በጉብኝታችን ወቅት ተመልክተናል::
በተሰጣቸው ጊዜ ገደብ ውስጥ ያልገነቡ እና የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓታቸውን ያላስተካከሉትን በመቅጣት ላይ የምንገኝ ሲሆን ከቅጣቱ በላይ የምንፈልገው ህዝባችን በዋናነት ለራሱ ጤና ሲል የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓቱን እና ብክለት መከላከልን እንዲተገብር በመሆኑ ሁላችንም ለዚህ ርብርብ እንድናደርግ ጥሪ አቀርባለሁ::
ያቀረብንላቸውን ጥሪ በመቀበል ህንጻዎችን በማደስ፣ ቀለም በመቀየር እና በከተማዋ ስታንዳርድ መሰረት መብራት በመዘርጋት እያገዙን የሚገኙ የከተማችን ነዋሪዎች፣ ባለሀብቶች እንዲሁም የመንግስትና የግል ተቋማትን ጨምሮ ሙያዊ እና ቁሳዊ ድጋፍ እያደረጉልን የሚገኙ ነዋሪዎቻችንን በራሴ እና በከተማ አስተዳደራችን ስም ላመሰግናቸው እወዳለሁ::
በቀሪ ጊዜያት ልዩ ክትትል በማድረግ ቶሎ መጠናቅ ያለባቸውን ስራዎች መጨረስ፣ መደገፍ የሚገባቸውን ደግሞ እየደገፍን ህዝባችንን በታማኝነት ለማገልገል በገባነው ቃል መሰረት 2ኛውን ምዕራፍ የኮሪደር ልማት አጠናቅቀን ለግልጋሎት ክፍት የምናደርግ ይሆናል::
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ