በዲጅታል ዕውቀትና ክህሎት የሰለጠነ ማህበረሰብ ለመፍጠር ኢትዮ-ኮደር ስልጠና ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ።
የልደታ ክፍለ ከተማ በሁለተኛው ዙር የአምስት ሚሊየን የኢትዮጵያ ኮደር ኢንሼቲቭ ስልጠናን አስመልክቶ ከክፍለ ከተማና ከወረዳ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።
የልደታ ክፍለ ከተማ ምክትል ስራ አስፈፃሚና ሰራና ክህሎት ጽ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ ነፃነት ደረሰ በመድረኩ ተገኝተው እንደተናገሩት በዲጅታል የታገዘ ማህበረሰብ ለመፍጠር ኢትዮ-ኮደር ስልጠና የማይተካ ሚና ስላለው እንደ ሀገር በኢትዮ-ኮደር ስልጠና ዜጎችን ለመጥቀም ታስቦ የስልጠና እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅሰው ይህን እስከታች ስልጠናውን መስጠት እንደሚገባ ገልፀዋል።
የኢትዮ - ኮደር ስልጠና እንዲሰጥ የተፈለገው ጊዜው የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ እንዲመጣ ለማድረግ ነው በማለት ወ/ሮ ነፃነት አያይዘው መንግስት ይህን እድል ለዜጎቹ በነጻ እንዲሠለጥኑ አመቻችቷል የመጣውን እድል ለመጠቀም በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ከክፍለ ከተማ እስከ ወረዳ የኢትዮ-ኮደር ስልጠና እድል ማህበረሰባቸው ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ በትኩረት መሰራት እንደሚገባ ወ/ሮ ነፃነት ደረሰ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የልደታ ክፍለ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገመቹ ጌታቸው እንደገለፁት
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ከግብ ለማድረስ እንደ አመራር ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የወጣቶችና የሴቶችን ተወዳዳሪነት በአምስት ሚሊዮን ኮደር ኢንሼቲቭ በማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በተለየ መረባረብ ይገባልም ብለዋል።
በሀገር ደረጃ አፅንኦት ተሰጥቶት በአራት ኮርሶች ስልጠናው እየተሰጠ እንደሆነ የገለፁት አቶ ገመቹ በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ አንድሮይድ ፕሮግራሚንግ፣ በዳታ ሳይንስ እና በሰውሰራሽ አስተውሎት (AI) ዋነኛ የትኩረት ነጥቦች ናቸው በማለት ይህን ስልጠና ወስደው ሲጨርሱ በዓለም ዓቀፍ ተቀባይነት ያለው ሰርተፍኬት ባለቤት እንደሚሆኑ ገልፀዋል።
ተሳታፊዎችም መድረኩ ኢትዮ-ኮደር ስልጠና ግንዛቤ የፈጠረ መሆኑን አንስተው በቀጣይ የመጣውን እድል በመጠቀም ማህበረሰብ በስልጠናው እንዲያልፍ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።